ብርታት እናግኝ፣ ተስፋን እንሰንቅ።
ታህሳስ 2016 ዓ.ም
የናዳን መልእክት በቀውስ ውስጥ ላሉ ሁሉ፤
...
ብርታት እናግኝ፣ ተስፋን እንሰንቅ።
...
እንደሚታወቀዉ በሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 3 ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረዉ እንዲሁም አሁን ላይ በአማራ ክልል በሚካሄደዉ ጦርነት ምክንያት በማህበረሰባችን ላይ የተለያዩ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለይም ጦርነት በማህበረሰባችን ሁለንተናዊ አኗኗር ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በከፋ ሁኔታ የስነ-ልቦና፣ የአዕምሮ ጤና እና ማህበራዊ ህይወት ላይ ምን ያክል ችግር እንደሚያስከትል ይታወቃል፡፡ አሁንም በምልከታ ጥናቶች እንደታየውና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ቃላቸዉን የሚሰጡ ግለሰቦች፣ በየአካባቢያችን የምናያቸዉ ሰወች እና የተቋማት ሪፖርቶች እንዲሁም የተለያዩ የጤና ባለሞያወች እንደደሚገልጹት፤ ይህ ሁኔታ ከባድ ቀውስን እያስከተለ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር ነው፡፡
በዚህ አስከፊ ጊዜ የስነልቦና የመጀመሪያ ድጋፍ መስጠት ለሁሉም አስፈላጊ ነው። የስነ ልቦና የመጀመሪያ ድጋፍ ለእኛ ሀገር ባህልና ወግ አዲስ ነገር አይደለም። በዚህ የውጥንቅጥ ጊዜ እርስበርሳችን አይዞን ልንባባል፣ በሁሉም የህይወታችን ክፍል ልንደጋገፍና የትኛውንም ውጥረትና ጭንቀት የሚያመጣ ነገር ልንጋፈጠው ያስፈልጋል።
ዓላማችን ምንም ይሁን፣ የማንም ደጋፊ ብንሆን፣ እስከየትኛውም ጥግ ለመሄድ ብንወስን መጀመሪያ የሚቀድመው ደህንነታችንና ጤናማ ማንነታችን ነው። ስለሆነም አካላዊ ማንነታችንን ከጉዳት፣ ከአደጋ እንደምንጠብቀው ሁሉ ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳይደርስብን ራሳችንን መጠበቅ አለብን።
ምንም አይነት ክፉ ነገር ቢደርስብን፣ ንግዳችን ኪሳራ ቢገጥመው፣ ያለምናቸው ነገሮች ባይሳኩ፣ ወገን ዘመድን በሞት ብንነጠቅ፣ ከአካላችን ብንጎድል፣ የምንበላው ብናጣ ግን በተስፋ እና በእምነት ጠንካሮች ሆነን እንድንሻገር ያሻል። ይህ ለሁሉ ቀላል አይደለም ነገር ግን የበረታ የደከመውን፣ የቀደመ የቀረውን፣ ከፍ ያለ ዝቅ ያለውን እየተረዳዳን ሰው ሆነን በህብረት እንድናልፍ ያሻል።
...
አይዟችሁ ይህ ድቅድቅ ጨለማ ያልፋል፣ ይህ አስጨናቂ ጊዜ ያልፋል፣ ይህ ያልተገባን ጊዜ ያልፋል። አይዟችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ፣ ትናንት እንደዚህ አይነትና ከዚህም የከፋ አስከፊ ጊዜ ነበረ፣ ከዚህ የባሰ መጠላላት ከዚህም የከፋ እርስበርስ መገዳደል ነበረ ያ ግን አልፎ መልካም ጊዜና ፍቅርም ከእኛ ጋራ ነበር። አሁንም አይዟችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ ይህ ሁሉ ጊዜ ያልፋል። በፍጹም እመኑ ከዚህ ሁላችንም ከማንወደው ተብትቦ ከያዘን ድንቁርና፣ ጥል፣ ዘረኝነት፣ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ ድህነት፣ ችግር፣ ጉስቁልና፣ ስንፍና ቀውስ፣ ሰቀቀን፣ ግፍ ሁሉ እንወጣለን። ሆኖም እንዲህ እያልን ቁጭ እንድንል አይደለም፤ ይልቁንም በመደጋገፍ ተያይዘን እንድንወጣ፣ ባመንንበትና በመልካሙ መንገድም ከዚህ ቀውስ እንድንሻገር እያንዳችን የበኩላችንን እንድንወጣ ያስፈልጋል።
...
ብርታትና ጽናት፣ ተስፋና እምነት ለሁሉም።
በዚህ ሰዓት ባለሙያዎች መሆን አይጠበቅብንም፣ ማንም ቢሆን አይዞን መባባልና ተስፋን መስጠት፣ መበረታታትና ተያይዘን ይህን ጦስ ማለፍ ያስፈልገናል። በርቱ ጠንክሩ።
...
ናዳን የልህቀት ማዕከል ባህር ዳር አባይ ማዶ ያለው ቢሮአችን ላይ ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ችግር የገጠማቸውን ሁሉ በነጻ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። በናዳን የስነልቦና፣ የስነ አእምሮ፣ የማህበረሰብ ጤና፣ ህክምና ባለሙያዎች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው።
ለጊዜው ኢንተርኔት ስለማይሰራ በስልክ ይጠቀሙ፥
0927958822
.jpg)
Comments
Post a Comment